29 May, 2025
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበላይ አመራሮች ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የበላይ አመራሮች ጋር በቀጣይ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
ለምክር ቤቱ በሥራና ክህሎት ሚነሰቴር የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ገለፃ የቀረበ ሲሆን፤ ምክር ቤቱ የጀመራቸውን የሪፎርም ስራዎችን አጠናክሮ መሥራት እንዲችልና ለተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፈጥር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በማተኮር የበላይ አመራሩ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሠ ጫፎ ሀገራችን ያላትንና ያልተጠቀምናቸውን እምቅ ሀብት በመጠቀም ከድህነት ለመላቀቅ እና የሀገራችንን ዕድገት ለማፋጠን የኢንተርፕረነር አስተሳሰብን መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ይህን ለማድረግ እንዲረዳ የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት የሚሠራቸው ሥራዎች ለውጥ የሚያመጡ ናቸው ያሉት የተከበሩ አቶ ታገሠ ከተለመደው አስተሳሰብ በመውጣት፣ አስቻይ አስተሳሰብን በማጎልበትና የሀብት ምንጮቻችንን በአግባቡ በመጠቀም ሀገራዊ ዕደገትን ለማፋጠን መሥራት ይገባል ብለዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል እንዳስረዱት ከተለመደው አሠራር በመውጣትና የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት ሀገራዊ ለውጥን ለማስቀጠል የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓትና የዲጂታል ትራንሰፎርሜሽን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
አያይዘውም የፈጠራና የክህሎት ሥራን የማሳደግ ተግባር ላይ ትኩረት በማድረግ በመንግሥት ደረጃ ትኩረት የተሰጠውን የኢንተርፕሪኒያል መንግሥት አሠራር ሥርዓትን መከተል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ተቋማትን ለማዘመንና የፈጠራ አስተሳሰብን ለማስረፅ የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንሰተትዩት የሚሠራውን ሥራ የበለጠ ውጤትማ ማድረግ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
የተከበሩ ምክትል አፈ-ጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሎሚ በዶ በበኩላቸው እንደሀገር ያሉንን ዕውቀቶች ተጠቅመንና አዳጋች የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ለውጥ ለማምጣት በተቋማት አቅም ግንባታ ላይ በቀጣይ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር የተከበሩ ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) እንደገለፁት ሀገራዊ የድህነት ሁኔታን ለመቀየር የሚያስችል ብዙ ሀብት እያለን ተመፅዋች መሆናችን እንደሀገር የሚመጥን አይደለም ብለዋል።
ስለሆነም የአስተሳሰብ ለውጥ ለማምጣት መትጋት እንዳለብንና ከዚህ አኳያ የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንሰተትዩት እየሠራው ባለበት መልኩ በሥራዎቻችን ፈጠራን በመጨመር ሀገራዊ ዕድገትና ብልፅግና ማምጣት ይገባል። ለዚህም ስራዎቻችንን የኢንተርፕርነርሺፕ ዕሳቤን በመጠቀም መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ ገልፀዋል።
በመጨረሻም በቀጣይም ምክር ቤቱ የጀመራቸውን ሪፎርም ሥራዎችን ይበልጥ አጠናክሮ ለማስቀጠልና አስቻይ ሁኔታዎች ለመፍጠር ሁለቱ ተቋማት በጋራ ጉዳዮች ላይ አብረው እንደሚሰሩ ሰፊ ውይይት በማድረግ ተጠናቋል፡፡
ዘገባው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።
© EDI 2026. All Rights Reserved. HTML Codex